የጨረራ ጠቀሜታዎች የጨረራ ጠቀሜታዎች

Return to Full Page

 

 
 
 
 

ጨረራ በአይን የማይታይ በሞገድ ወይም በልዩ ልዩ ቅንጣጢቶች መልክ ከቦታ ቦታ የሚጓዝ ሃይል ነው፡፡ ጨረራ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ መንገድ ልናገኘው እንችላለን፡፡

በዛሬው ጽሁፍ የሰው ሰራሽ ጨረራን ጠቀሜታን ለማስተዋወቅ እንሞክራለን፡፡ ጨረራ በአለማችን ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቴክኖሎጅ ከመሆኑ የተነሳ የአገራት የታላቅነት ሚስጢር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ለዚህም የአሜሪካ ፣ ሩሲያ ፣ ቻይና ፣ ሰሜን ኮሪያን ነባራዊ ሁነታ ማየት እንችላለን፡፡ ሀገራቱ የሚፈሩትና የሚከበሩበት ዋነኛው ሚስጢር የኑክሌር ሃይል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

 
 
 
 
 

ጨረራ በርካታ ሰላማዊ ጥቅሞችን የሚሰጥ ሲሆን ለጥፋት መሳሪያነትም ከተጠቀሙበት አደጋው የከፋ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር መሆኑንም እንመለከታለን ፡፡ ለአብነት በአንድ ወቅት አሜሪካ በጃፓን ሄሮሺማና ነጋሳኪ ያደረሰችው ጥፋት እስከ ዛሬ ድረስ በአካባቢና በትውልዱ ላይ ጠባሳው አልጠፋም፡፡ ምንም እንኳን ጨረራን ለጦር መሳሪያነት መጠቀም ለማገድና ለመቆጣጠር እንደ አለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጅ ኤጀንሲ ያሉት ተቋማት ብዙ እየሰሩ ቢሆንም የኑክሌር የጦር መሳሪያን ብዙ ሀያላን ሀገራት ታጥቀውት ይገኛሉ፡፡ የዛሬው ጽሁፍ አላማ የጨረራን ሰላማዊ ጠቀሜታ መዳሰስ ሲሆን የጨረራን ጠቀሜታ ለየት የሚያረገው ጨረራ የማይዳስሰው ዘርፍ አለመኖሩ ነው፡፡ ይህንን እውነታ በተግባር ለማሳየት የተወሰኑትን ጠቀሜታዎች ማንሳቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

 
 
 
 
 

ለኤሌክትሪክ ሃይል አማራጭነት፡- ጨረራ ለኤሌክትሪክ ሃይል አማራጭነት ያለው ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ዘርፍ አፍሪካ እንደ አህጉር ተጠቃሚነቷ ብዙ የሚባልበት ባይሆንም ሌሎች አህጉራት በተለይ ያደጉት አገራት የኑክሌር ሃይል ማብላያ ጣብያ በመገንባት ከፍተኛ የኑክሌር ሃይል በማምረት አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እያገኙ ያገኛሉ፡፡ ዛሬ በአለማችን ላይ ከ442 የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች 383,513 ሜጋ ዋት የተጣራ የኤሌክትሪክ ሃይል በመመረት ላይ ሲሆን በቀላል ስሌት አንድ ኑክሌር ማብላያ ጣቢያ በአማካኝ 868 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመርታል ማለት ነው፡፡ የኑክሌር ማብላያ ጣቢያ ስርጭትን ስንመለከት አሜሪካ 99 ፣ ፈረንሳይ 58 ፣ ጃፓን 43 ፣ ሩሲያ 35 ፣ ቻይና 31 እና ኮሪያ 25 በመያዝ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው የሚጠቀሱ ሲሆን ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ 2 የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች ያላት ብቸኛ ሀገር ናት፡፡

 
 
 
 
 

በሽታን ለመመርመርና ለማከም፡- ዛሬ ዛሬ ያለጨረራ መሳሪያ የህክምና ስራ ማካሄድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ይመስላል፡፡ በቀላሉ ለመጥቀስ የውስጥ አካል ችግርን ለመለየት ከምንጠቀምበት ራጅ ጀምሮ ሲቲ ስካን፣ ማሞግራፊ፣ ኒውክለር ሜዲሲን፣ ራዲዮቴራፒ፣ ራዲዮአይሶቶፕስ፣ ሪሰርች ሪአክተር የመሳሰሉት ልዩ ልዩ የጤና እክሎችን፣ ካንሰርንና መሰል ችግሮችን ለመለየትና ለማከም የጨረራ ቴክኖሎጅ በህክምና ዘርፍ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

 
 
 
 
 

የምርት ጥራትን ለመፈተሸና ለመቆጣጠር፡- የጨረራ ቴክኖሎጅ በኢንዱስትሪውና በኮንስትራክሽኑ አካባቢ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ሲሆን በዋናነት የምርት ጥራትን ለመፈተሽና ለመቆጣጠር ይጠቅማል፡፡ በመጠጥ ፋብሪካዎች የሚታሸጉ ምርቶች በእኩል ደረጃ እንዲታሸጉ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁ የሚደባለቁ ጥሬ ምርቶችን አይነት፣ ይዘትና ጥራት ለመቆጣጠር፣ በመንገድ ስራዎችና በልዩ ልዩ ግዙፍ ግንባታዎች (ህዳሴ ግድብ) የመንገዶችንና ግድቡን እርጥበትና ጥቅጥቃት ወይም ጥራት ለመቆጣጠር የምንጠቀመው ልዩ ልዩ ኑክሌር ጌጆች የጨረራ ቴክኖሎጅዎች ናቸው፡፡

 
 
 
 
 

የግብርና ምርታመነትን ለማሳደግ፡- የጨረራ ቴክኖሎጅ ሌላው በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝበት ዘርፍ የግብርናው መስክ ሲሆን የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በዚህ ዘርፍ ምርጥ ዘርን ለማግኘት በሚደረገው ምርምር፣ የመሬትን ባህሪ ለማጥናትና የውሃና የማዳበሪያ አጠቃቀምን ለማወቅ፣ አላስፈላጊ የቆሻሻ ፍሳሾችን ለማስወገድ፣ የግብርና ምርቶች ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩና እንዳይበሰብሱ ለማድረግ፣ ከምግብ እህሎች ጎጅ ነፍሳትን፣ ባክቴሪያዎችንና ማይክሮ ኦርጋኒዝሞችን ለማጥፋት ወዘተ የጨረራ ቴክኖሎጅ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

 
 
 
 
 

ለሳይንስ ትምህርት ምርምርና እድገት፡- የሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በኑክሌር ዘርፍ ከፍተኛ የምርምር ስራዎችን ለመስራት የሚረዳው ሪሰርች ሪአክተር የሚባለው የጨረራ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ መሳሪያ በኒውትሮን ምርት በህክምናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ራዲዮአይሶቶፖች ከማምረት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለአርኪዮሎጅካልና ጅኦሎጅካል ምርምር፣ ለግብርናው ዘርፍ፣ ለኒውክለር ፊዚክስ፣ ለሜዲካል ፊዚክስ፣ ለኒውክለር ሜዲሲን፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፍና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል፡፡

 
 
 
 
 

ለቴሌኮሙኒኬሽንና መገናኛ ዘርፍ፡- በሁላችን እጅ ያለችው የሞባይል ስልክ በጨረራ ቴክኖሎጅ በመታገዝ የምትሰራ ነች፡፡ የሞባይል ስልክ አዮን የማይፈጥር ጨረራ አይነት ሲሆን ለአለማችን እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

 
 
 
 
 

ለፍተሻና ደህንነትን ለማረጋገጥ፡- ዛሬ ዛሬ በአለማችን ላይ ትላልቅ ሁነቶች ለምሳሌ እንደ አለም ዋንጫ እና ሌሎች መሰል ሁነቶችን የሚያስተናግዱ ሀገራት ትልቁ ስጋታቸው የሰዎች ደህንነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጨረራ መፈተሻ መሳሪያዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ አደገኛ የጨረራ ቁሶችንና ሌሎች ባእድ ቁሶችን ለመለየት አገልግሎት ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው፡፡